የጋራ ሚዲያ መግለጫ በአሪፍፔይ እና ኢትስዊች

  • Home
  • የጋራ ሚዲያ መግለጫ በአሪፍፔይ እና ኢትስዊች

የአሪፍፔይ እና የኢትስዊች ጥምረት በተናባቢነት ለደንበኞች፤ ለነጋዴዎች እና ለባንኮት በርካታ ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል፡፡

አሪፍፔይ ከኢትስዊች ጋር ያደረገው ጥምረት ለኢትዮጲያ የፋይናንሺያል አካታችነት መንገድ ከፋች ነው!

በኢትዮጵያ ቀዳሚ የክፍያ ስርዓት ኦፕሬተር (PSO) የሆነው አሪፍፔይ በሀገሪቱ የክፍያ ኢንደስትሪ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሆነውን እርምጃ በመውሰድ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የክፍያ ስዊች (ኢትስዊች) ጋር ጥምረት መፍጠሩን አስታወቀ። ይህ አጋርነት ለደንበኞች፣ ለነጋዴዎች እና ለባንኮች በርካታ ጥቅሞችን ይዞ የሚመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንሺያል አካታችነት እና የክፍያ ሥርዓቶችን ለማሻሻል የታሰበ ነው፡፡

ይህ ጥምረት ደንበኞች በኢትስዊች ኔትወርክ አማካኝነት የየትኛውንም ባንክ ካርድ በመጠቀም በArifPOS ግብይት እንዲያደረጉ በማስቻል ምቹ እና ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ነጋዴዎችም ከተለያዩ ባንኮች የሚቀርቡላቸውን የPOS መሳሪያዎችን ከመጠቀም በአማራጭነት የቀረበውን አንድ የArifPOS መሳሪያ ብቻ በመያዝ ከአሪፍፔይ የንግድ አጋሮች የሚቀርቡላቸውን ተጨማሪ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል።

በሌላ በኩል ጥምረቱ ባንኮች በዋና የስራ ዘርፋቸው ላይ እንዲያተኩሩ እና ወጪአቸውን በመቆጠብ ከፍተኛ የሃገር ዉስጥ እና የዉጭ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ያስችላቸዋል።

በአሪፍፔይ እና ኢትስዊች መካከል ያለው ጥምረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ምክንያቶቹም የሚከተሉት ናቸው።

  1. የፋይናንሺያል አካታችነትን መጨመር፡- የዚህ ጥምረት ቁልፍ ጥቅሞች ከሆኑት መካከል አንዱ የየትኛውንም የኢትዮጵያ ባንኮች የክፍያ ካርድ የያዙ ደንበኞችን በአሪፍፔይ “POS” ተርሚናሎች ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ በኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎትን እንዲያገኙ ማስቻል ነው። ይህም ብዙኋኑን ወደ መደበኛው ኢኮኖሚ ለማምጣት ይረዳል፣ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገትን ይደግፋል።
  2. ፈጣን የክፍያ ስርዓት፡ ይህ አሰራር ለግብይት የሚዉል ጊዜን በመቀነስ እና የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትን በማጥፋት የክፍያ ሂደቱን የበለጠ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ ያደርገዋል። ይህም የንግድ ሥራዎችን በፍጥነት እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲካሄዱ በማስቻል የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ይረዳል።
  3. የተሻሻለ ግንኙነት (Inter-connectivity)፡ ይህ በአሪፍፔይና በኢትስዊች መካከል የተፈጠረው ትስስር የኢትዮጲያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ እንከን የለሽ የተሳለጡ ግብይቶችን በመፍጠር ለአጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱ መረጋጋትና መሻሻል እንዲኖር ይረዳል።
  4. ለአነስተኛ ጥቃቅን ንግዶች ድጋፍን ማመቻቸት፡ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የክፍያ አማራጮችን በማቅረብ፣ አነስተኛ ንግዶች የገንዘብ ፍሰታቸውን በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደር እና የንግድ ልውውጦችን እንዲያደርጉ በማስቻልና ተጨማሪ የስራ እድሎችን በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ይረዳል።

ኢትስዊች እንደዚህ ያሉ አዳዲስ ሃሳቦች ለመደገፍ ያለውን ዝግጁነት እንዲሁም የፋይናንሺያል ኣካተችነትን በማበረታታት እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው። በዚህ ረገድ የአሪፍፔይ ከኢትስዊች ጋር መጣመር በፋይናንሺያል ሴክተር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻዎች እንዴት ደንበኞችን እና ሰፊውን ኢኮኖሚን የሚጠቅሙ መፍትሄዎችን መፍጠር እንደሚችሉ ዋና ማሳያ ነው።

የኢትስዊች ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይለበስ አዲስ በበኩላቸው “ኢትስዊች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተሳትፎን በሚያበረታቱ ጅምሮች ላይ ግንባር ቀደም በመሆኑ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፤ እኛም አሪፍፔይን ከኢትስዊች ጋር ለማስተሳሰር ድጋፍ ስናደርግ ደስተኞች ነን” ሲሉ አጋርነታቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ገልጸዋል።

የአሪፍፔይ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በርናርድ ላውረንዶ በሰጡት ምላሽ ይህ አጋርነት በተጠቃሚዎች የእለት ተእለት ህይወት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጠቀሜታ በማንሳት “በተናባቢነት (Interoperability) የሚሰሩ አሪፍፔይ “Smart POS” በማመቻቸት በኢትዮጵያ ያሉ ሸማቾች ለእለት ተእለት ክፍያ ተጨማሪ አማራጮችን ያገኛሉ” ብለዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ደንበኞች የዴቢት ካርዶቻቸውን በኤቲኤም ብቻ ለመጠቀም አይገደቡም ሲሉም አክለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጆቹ እንደገለጹት በአሪፍ ፔይ እና ኢትስዊች መካከል ያለው አጋርነት በኢትዮጵያ ፋይናንሺያል አካታችነትን በማስተዋወቅ አንዲሁም በማስቀጠል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማበረታታት ያለውን ጠቀሜታ አመላካች ነው።


ለተጨማሪ መረጃ ወ/ት ትንሳኤ ተፈሪ፣ የአሪፍፔይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያናግሩ።
tinsae@arifpay.net
+251902145801